አሰልበርህት
አሰልበርህት (552 -608 ዓ.ም.) ከ572 ወይም 582 ዓ.ም. አካባቢ እስከ 608 ዓ.ም. ድረስ የኬንት ንጉሥ ነበረ። ከእንግሊዝ ንገስታትም መጀመርያው የተጠመቀ እሱ ነበር። ስለዚህ በሮማ ካቶሊክ፣ በምሥራቅ ኦርቶዶክስና በአንግሊካን ሃይማኖቶች «ቅዱስ» ይባላል።
በአንግሎ-ሳክሶን ዜና መዋዕል ዘንድ፣ እሱ አባቱን የኬንት ንጉሥ ኤዮርመንሪክን ተከተለ። የፍራንኮች ንጉሥ ቻሪበርት ልጅ ቤርታን አገባት። እሷ ክሪስቲያን ነበረችና ከዚህ የተነሣ ንጉሥ ተጠምቆ ክርስትና በእንግሊዝ ሕዝብ መካከል ይፋዊ ሆነ። አውግስጢኖስ ዘካንተርቡሪ ከሮማ በ589 ዓ.ም. ተልከው የእንግሊዝ ሕዝብ መጀመርያ ሊቀ ጳጳስ ሆኑ።
አሰልበርህት ከኬንት በላይ በዘመኑ መጨረሻ በሌሎች የእንግሊዝ ደሴት መንግሥታት በኤሴክስና ምሥራቅ ኤንግላ ላይ ገዥነት ነበረው። በእርሱ ተጽእኖ የኤሴክስ ንጉሥ ሳበርህት እና የምስራቅ ኤንግላ ንጉስ ራድዋልድ በ596 ዓም ግድም ተጠመቁ።
በተጨማሪ በ594 ዓ.ም. ንጉሥ አሰልበርህት ለአገሩ ሕገ መንግሥት አወጣ። ይህ ሕገ መንግሥት በሮማይስጥ ሳይሆን የተጻፈው በጥንታዊ እንግሊዝኛ ነበረ። በኋላ ዘመን የእንግሊዝ ንጉሥ ታላቁ አልፍሬድ ከዚህ ሕገ መንግሥት ወስደው የተሻሸለ ሕገ መንግሥት አወጡ።
አሰልበርህት በ608 ዓ.ም. ካረፈ በኋላ ልጁ ኤድባልድ ተከተለው። ኤድባልድ ግን በመጀመርያ ወደ አረመኔነት ቢመልስም በኋላ ግን ክሪስቲያን ንጉሥ ሆነ።
በአሰልበርህት ሕግ ፍትሕ ግድያ፣ ስርቆት፣ ዝርፍያ፣ ትግል፣ የሀብት ወይንም የሰውነት ጉዳት፣ ማመንዝር፣ ስላምን ማጥፋት ያደረጉ ሁሉ የገንዘብ መቀጮ ወይም ካሣ ነበረባቸው። የመቀጮው መጠኖች ግን እንደ ተበዳዩና በድለኛው መደቦች ወይም ማዕረጎች ልዩነት ትክክል አልነበሩም። ከሁሉ የተጠበቀው የቤተ ክርስቲያን ነዋይ ነበር፤ ፲፪ እጥፍ ካሣ ነበረበት። እንዲሁም ሁከት በሆነበት ጊዜ ለሰው መሣርያን መስጠት በገንዘብ መቀጮ ተከለከለ።
ይህ ሕግ ፍትሕ የማጫ ሥርዓት እንዲህ ይቀምራል፦
« ስው ሳዱላን በማጫ ቢታጭ፣ (ንብረቱ) እንከን የለሽ ቢሆን የታጩ ይሁኑ። ነውሩ ቢሆን፣ በኋላ ወደ ቤቱ ያምጣው፣ ሰውም በገንዘብ ይስጠው። እርሷ ሕይወት ያለ ልጅ ከወለደች፣ ባልም (ከርስዋ) አስቀድሞ ቢሞት፣ ግማሽ ገንዝብ ትይዝ።... እርስዋ ልጅ ካልወለደች፣ የአባትዋ ቤትሠብ ሀብቱን ጥሎሽንም ይይዙ። ሰው ሳዱላን በወሲብ ቢወስድ፣ ለጠባቂዋ ፶ ሺሊንግ (የወርቅ መሃለቅ) ይካሥ፣ በኋላም የጠባቂዋ ፈቃድ እንደ ሆነ ይታጫት። እርስዋ ለሌላው በገንዘብ የታጨች ብትሆን፣ (ተጨማሪ) ፳ ሺሊንግ ይካሥ። ብትመለስ፣ ፴፭ ሺሊንግ፣ ለንጉሥም ፲፭ ሺሊንግ።»
- የአሰልበርህት ሕግጋት በሙሉ Archived ሴፕቴምበር 9, 2013 at the Wayback Machine (በጥንታዊ እንግሊዝኛ እና በዘመናዊ እንግሊዝኛ ትርጉም)