Jump to content

የላቲን አልፋቤት

ከውክፔዲያ
(ከላቲን አልፋቤት የተዛወረ)
አረንጓዴ፦ የሀገሩ ይፋዊ ቋንቋ(ዎች) በላቲን ፊደል ይጻፋል።
ክፍት አረንጓዴ፦ ላቲን ፊደል ከሌሎች ጽሕፈቶች ጋር ይፋዊ ነው።

የላቲን አልፋቤት ወይም ሮማዊው አልፋቤት በመጀመርያው ሮማይስጥን ለመጻፍ የተለማ ጽሕፈት ነው። ዛሬው በዓለም ዙሪያ ይገኛል፣ በዓለም ከሚገኙት ልሣናት መካከል ብዙዎቹ የሚጻፉ በላቲን ፊደል ወይም ከላቲን ፊደል በተደረጀ ፊደል ነው።

ከላቲን ፊደል ቀድሞ፦ ጥንታዊ ኢታሊክ ፊደል

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

መጀመርያው ላቲን አልፋቤት በቀጥታ ከጥንታዊ ኢታሊክ አልፋቤት በተለይም ከኤትሩስክኛው አልፋቤት ተወሰደ። ይህም ኢታሊክ አልፋቤት በፈንታው ከጥንታዊው ምዕራብ ግሪክ አልፋቤት በተለይም ከኩማይ አልፋቤት ተለማ።

በሮማውያን አፈ ታሪክ ሁጊኑስ 1 ዓም አካባቢ እንደ ጻፈው፣ ኤቫንደር የተባለው ጀግና ምናልባት 1240 ዓክልበ. የግሪክ አልፋቤት ወደ ጣልያን አስገባ፣ ከዚያም እናቱ ሲቡሊቷ ካርሜንታ 15ቱን ፊደላት ወስዳ የላቲን አልፋቤት ፈጠረች። ነገር ግን ይህ ተረት እንደ ታሪካዊ አይቆጠረም።

ጥንታዊ ኢታሊክ አልፋቤት (ኤትሩስክኛ) እስከ 600 ዓክልበ. ግድም (27 ፊደላት)
ፊደላት 𐌀 𐌁 𐌂 𐌃 𐌄 𐌅 𐌆 𐌇 𐌈 𐌉 𐌊 𐌋 𐌌 𐌍 𐌎 𐌏 𐌐 𐌑 𐌒 𐌓 𐌔 𐌕 𐌖 𐌗 𐌘 𐌙 𐌚
ድምጽ ክስ

እስከ 600 ዓክልበ. ግድም ድረስ ደግሞ የጽሕፈቱ አቅጣቻ ወይም ከግራ ወደ ቀኝ፣ ወይም ከቀኙ ወደ ግራ ሊሆን ቻለ። ከላይ ያለው ሠንጠረዥ ከግራ ወደ ቀኝ ሲጻፉ የነበራቸውን መልክ ያሳያል። ቀስ በቀስ ከ600 ዓክልበ. ግድም በኋላ እስከ 400 ዓክልበ. ግድም ድረስ፣ የኤትሩስክኛ አጻጻፍ ሁልጊዜ ከግራ ወደ ቀኙ መሄዱ መደበኛው ልማድ ሆነ።

ደግሞ በነዚህ ዘመናት ላይ (600-400 ዓክልበ. ያሕል) ኤትሩስክኛን ለመጻፍ የ፮ቱ ፊደላት - 𐌁 𐌊 𐌎 𐌏 𐌒 𐌗 - በጥቅም ተግባራዊ አልነበሩም። ሆኖም ከ«𐌎» በቀር እነዚህ ሁሉ በሮማይስጥ ቆዩ።

ጥንታዊ ላቲን (ሮማይስጥ) ፊደል

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ሮማይስጥን ለመጻፍ ግን ስድስቱ ፊደላት፤ 𐌈 (ጥ)፣ 𐌎 (ሽ)፣ 𐌑 (ሥ)፣ 𐌘 (ጵ)፤ 𐌙 (ሕ)፣ 𐌚 (ፍ) አስፈላጊ ስላልሆኑ፣ ከአልፋቤት ተወገዱና መጀመርያው የላቲን አልፋቤት 21 ፊደላት ብቻ ነበረ፦

መጀመርያው ላቲን አልፋቤት እስከ 320 ዓክልበ. ግድም (21 ፊደላት)
ጥንታዊ ኢታሊክ ቅርጽ 𐌀 𐌁 𐌂 𐌃 𐌄 𐌅 𐌆 𐌇 𐌉 𐌊 𐌋 𐌌 𐌍 𐌏 𐌐 𐌒 𐌓 𐌔 𐌕 𐌖 𐌗
ዘመናዊ ቅርጽ A B C D E F Z H I K L M N O P Q R S T V X
ድምጽ ግ፣ ክ ኢ፣ ይ ኡ፣ ው ክስ

«ክ» የሚለውን ድምጽ ለመጻፍ በ«C»፣ «K»፣ ወይም በ«Q» የተጻፈው ሲሆን፣ አብዛኛው ጊዜ እንደ አናባቢው ይለያይ ነበር፣ እንዲህ፦ KA ካ፣ CE ኬ፣ CI ኪ፣ CO ወይም QO ኮ፣ QV ኩ።

በ400 አክልበ. አካባቢ ጥንታዊ ቅርጹ 𐌑 ለ/ሥ/ በሮማይስጥ ስላልጠቀመ የ𐌌 /ም/ ቅርጽ ወደ «M» ተለወጠ፤ እንዲሁም ቅርጾቹ 𐌇 /ህ/ እና 𐌍 /ን/ እንደ ዘመናዊ ቅርጾቻቸው H እና N ይጻፉ ጀመር። ለነዚህም ሁሉ (H, M, N) ተመሳሳይ ለውጦች በግሪኩ አልፋበት ደርሰው ነበር። እንዲሁም እንደ አንዳንድ ምዕራባዊ ግሪክ አልፋቤቶች በመምሰል፣ 𐌓 /ር/ ወደ R እና 𐌖 /ኡ/ ወይም /ው/ ወደ V ሊቀየሩ ጀመር።

በአንዳንድ መዝገቦች ዘንድ፣ የሮሜ ኬንሶርና አምባገነን አፒዩስ ክላውዲዩስ ካይኩስ በ320 ዓክልበ. «Z»ን ስላልወደደ ከላቲን ፊደል እንደ ጣለው ይባላል።

በ230 ዓክልበ. ግድም፣ አስተማሪው ስፑሪዩስ ካርቪሊዩስ ሩጋ የ«ክ» ከ«ግ» ድምጽ ለመለየት፣ «C» ትንሽ በመለውጥ አዲስ ፊደሉን «G» እንደ ፈጠረ ይባላል። ከዚህ ጀምሮ C ለ«ክ» ብቻ፣ G ለ«ግ» ብቻ ይበቃቸው ነበር። በዚህ ወቅት ፊደሎች ደግሞ እንደ ቁጥሮች ስላገለገሉ የሌሎቹን ፊደላት ቁጥሮች ለመጠብቅ አዲሱ ፊደል «G» በቀድሞው «Z» ፋንታ በመተካት በ፯ኛው ሥፍራ ተሰካ።

ስለዚህ ከ230 ዓክልበ. ጀምሮ የላቲን ፊደል ኢንዲህ ሆነ፦

ላቲን አልፋቤት 230 ዓክልበ.-90 ዓም ግድም (21 ፊደላት)
ቅርጽ A B C D E F G H I K L M N O 𐌐 / P Q R S T V X
ድምጽ ኢ፣ ይ ኡ፣ ው ክስ

በሮሜ ንጉሥ ክላውዲዎስ (33-46 ዓም የገዛው) ትዕዛዝ፣ ሦስት አዳዲስ ፊደላት ተጨመሩ፦ «» (/ፕስ/)፣ «» (/ው/፤ ከ V /ኡ/ እንዲለይ)፣ እና «» (/ኢው/፣ በግሪክ ቃላት) ነበሩ። ሆኖም እነኚህ «የክላውዲዎስ ፊደላት» ከክላውዲዎስ ዘመን በኋላ አልቀሩም። በዚሁ ዘመን ግን ከ43 ዓም ያህል ጀምሮ፣ /ር/ እንደ R ስለ ተጻፈ፣ 𐌐 /ፕ/ እንደ ቀድሞ /ር/ በመምሰል እንደ «P» ሊጻፍ ጀመረ።

ጸሐፊው ኲንቲሊያን በጻፈው ኢንስቲቱቲዮ ኦራቶሪዮ በጻፈበት ወቅት (85 ዓም)፣ «X» ገና መጨረሻው ፊደል ይባል ነበር፣ ሆኖም በዚያው ጽሁፍ ዘንድ፣ በተለይ ግሪክኛን ቃላት ለመጻፍ ሁለት ፊደላት ከግሪክ (Y እና Z) ዳግመኛ እንዲጨመሩ የሚል አሣብ አቀረበ። ከዚያ በኋላ የላቲን ፊደላት ቁጥር 23 ሆነ፦

ላቲን አልፋቤት 90-500 ዓም ግድም (23 ፊደላት)
ቅርጽ A B C D E F G H I K L M N O P Q R S T V X Y Z
ድምጽ ኢ፣ ይ ኡ፣ ው ክስ ኢው

በኋላ የተጨመሩት ፊደላት

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የትንንሾቹ ፊደላት ልማድ ቀስ በቀስ በ400 እና 770 ዓም መካከል ተለማ። እነርሱም አሁን፦ abcdefghijklmnopqrstuvwxyz ናቸው።

ፊደሉ «V» ወይንም /ኡ/ ወይንም /ው/ ሊወከል ይችል ነበር። ከ600 ዓም በኋላ በጀርመናዊ ቋንቋዎች ውስጥ ድምጹን /ው/ ለመጻፍ፣ ይደረብ ነበር እንደዚህ፦ VV። በየጥቂቱ ከ1500 በፊት የራሱ ፊደል W ተቆጠረ።

ፊደሉ «V» ደግሞ /ቭ/ ለመጻፍ ቻለ። ቅርጹም ከ«U» ጋር ይለዋወጥ ነበር። ከ1378 ዓም በታየ በአንድ አልፋቤት ለመጀመርያው ጊዜ «U» እና «V» እንደ ልዩ ልዩ ፊደላት ተቆጠሩ። በ1754 ዓም የፈረንሳይ አካደሚ በይፋ «U» እና «V» እንደ ልዩ ልዩ ፊደላት ይቆጥራቸው ጀመር።

ከ1516 አስቀድሞ፣ የላቲን ፊደል «I» ለተነባቢው «ይ»፣ ለአናባቢው «ኢ» ተጠቀመ። ሆኖም በቃል መጨረሻ ሲደረብ እንደ -ii ሲጻፍ፣ ቅርጹ እንደ -ij ይምሰል ጀመር። ከ1516 ዓ.ም. ጀምሮ ቅርጹ «J» ለተናባቢው «ይ» እና ቅርጹ «I» ለአናባቢው «ኢ» ይለያዩ ጀመር። ይህም ልዩነት በእንግሊዝኛ («ጅ» ከ«ኢ/አይ» ለመለየት) ከ1625 ዓም ኖሯል።

ከነዚህ ሦስቱ አዳዲስ ፊደላት (J, U, W) ጋራ፣ ዘመናዊው ላቲን ወይም እንግሊዝኛው አልፋቤት በሙሉ 26 ፊደላት ይቆጠራሉ፦

ዘመናዊ 26 ፊደላት ዋና አጠራሮች
ቅርጽ A B C D E F G H I J K L M N O P Q R S T U V W X Y Z
ጣልኛ ክ፣ ች ግ፣ ጅ (-) ኢ፣ ይ - - ስ፣ ዝ ኡ፣ ው - - -
ፈረንሳይኛ ክ፣ ስ ኤ፣ እ ግ፣ ዥ (-) (ክ) (ው) ክስ
እስፓንኛ ክ፣ ግ፣ ሕ (-) (ክ) (ብ፣ ው፣ ጒ) ክስ፣ ስ፣ ሕ፣ ሽ
እንግሊዝኛ ኣ፣ ኤ ክ፣ ስ ኧ፣ ኢ ግ፣ ጅ እ፣ ኢ፣ አይ ኦ፣ አ ኡ፣ ኧ ክስ ይ፣ እ፣ አይ
ጀርመንኛ ብ፣ ፕ ክ፣ ጽ ድ፣ ት ኤ፣ ኧ፣ እ ግ፣ ክ ኢ፣ እ ኲ፣ ክቭ ስ፣ ዝ፣ ሽ ክስ ኢው
  • (-) ማለት ፊደሉ አይሰማም (H በጣልኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ እስፓንኛ)
  • ( ) ማለት ተራ ያልሆነ (በተለይ ለባዕድ ቃላት የሚጠቀም) (K, W በፈረንሳይኛ፣ እስፓንኛ)
  • - ማለት ፊደሉ በተግባር አይገኝም (J, K, W, X, Y በጣልኛ)

ይህ ሰንጠረዥ በቀላሉ ዋና ዋና አጠራሮች ለ5 ትልልቅ የአውሮጳ ቋንቋዎች ያሳያል። ሆኖም ከዚህ በላይ በጣም ብዙ ልዩ ድምጾች በሁለት (ወይንም በሦስት) ፊደላት ይመለከታሉ፣ ለምሳሌ በእንግሊዝኛ «SH» ለ/ሽ/ ይጻፋል። ከነዚህ 26 ተራ ፊደላት በላይ ደግሞ አያሌ ቋንቋዎች የራሳቸውን ልዩ ፊደላት አላቸው፤ ለምሳሌ በእስፓንኛው አልፋቤት ተጨማሪው ፊደል «Ñ» (/ኝ/) አለ፤ ወይም «Þ» (//) በአይስላንድኛ አለ።